በቤይሩት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉድ አመጣ
ዜጎችን አሳልፎ መሸጥ፣ ሰድቦ፣ ደብድቦ ማባረር ተክኗል…ዲያቆኑ ካድሬ ነው ያስቸገረን…
በግሩም ተ/ሀይማኖት
በአረብ ሀገራት ያሉ ኤምባሲዎች ለዜጎቻቸው የሚሰጡት አገልግሎት ከበፊቱ ትንሽ ለውጥ እያሳየ ነው የምንልበት ደረጃ ደርስን ነበር፡፡ መጠነኛ ለውጥ ካሳዩት ውስጥ ኩዌት አንዱ ነው፡፡ ቤይሩት ትንሽ ደህና ይሆኑና መለሰው ጭካኔያቸውን አሳድገው ብቅ ይላሉ፡፡ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዱባይ፣ ኳታር…ኤምባሲ አለ ወይ እስኪያስብል ባዶ ናቸው፡፡
በአረብ ሀገራት ያሉ ኤምባሲዎች ውስጥ የሚመደቡ ሰዎች ራሳቸው ዲፕሎማት መሆናቸውን አውቀው የዲፕሎማት መብታቸውን እንኳን መጠቀም የሚችሉ አይደሉም፡፡ በትምህርት ብቃት ኖሯቸውም ስላልሆነ የሚቀጠሩት የዲሎማሲያዊ ስራ አይሰሩም፡፡ መብታቸውንም አያውቁትም፡፡ ፖሊስ መንገድ ላይ አስቁሞ ያለመጥሪያ ይዞ ቢያንበረክካቸው የሚንበረከኩ ከትምህርት እና ከዲፕሎማሲ እውቀት ነጻ ናቸው፡፡ አንገታቸውን ደፍተው ተሸቆጥቁጠው ሲታዩ ምጽዋት የሚጠብቁ እንጂ ለዲፕሎማት ስራ የሚሄዱ አይመስሉም፡፡ በየሴቱ ቤት ሲዞሩ ግን ደረት አነፋፋቸው እና መወጠራቸው ሲታይ በስልጣን ከጠቅላይ ሚኒስትሩም በላይ የሆኑ ይመስላሉ፡፡
ህዝቡ መሀል ተሰግስገው ምስኪን መስለው የሚሰልሉ ዞረው ስድተኛውን የሚበድሉ ካድሬዎቻቸውም ሞልተዋል፡፡ የመን ህዝቡ መሀል ተመሳስለው ህዝቡን እየሰለሉ የኖሩት ቁጥር ከሌሎች አረብ ሀገራት በጣም በእጥፍ ነው፡፡ እኔም ሰነዓ በመጣሁበት ጊዜ እስር ቤት እያለሁ ሊሰልለኝ እስረኛ መስሎ ገብቶ የሰለለኝ ሰው ነበር፡፡ ሲሳይ የሚባል ሆቴል ያለው ሰው ምንም በማያውቀው አብሮት እንዲታሰር ተደርጎ ሲሰልለኝ አውቄ የተዛባ መረጃ ሰጠሁት፡፡ ይህ ሰው አለሙ የሚባል ትግሬ አሁን የመን ያለ ኤምባሲ ስለተዘጋ ኳታር ተቀይሮ ነው ያለው፡፡ ኳታሮች ጠንቀቅ በሉ አለሙ የሚባል ቫይረስ መሀላችሁ ገብቷል፡፡
ምን ማለቴ ነው፡፡ ወገናቸውን ከማዳን ይልቅ ጠልፈው ለመጣል ለመሰለል ነው የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በአረብ ሀገራት የሚጠነክሩት፡፡ ተመሳሳይ ወገናቸውን ከማገልገል ይልቅ ያስመረሩ በየቦታው አሉ፡፡ ቤይሩትም ያለ ኢትዮጵያዊ የሚማረርበት አንድ በድቁና ስም የሄደ ሰው አለ፡፡ ስደተኛውን ፍዳ የሚያበላ ከኮሚኒቲ ጀምሮ ኤምባሲውና ቆነስላው ደረስ ሁለገብ ነኝ የሚል ሰው ነው፡፡ በአንድ ወቅት ህሊና የምትባል ልጅ ከካናዳ የተወሰኑ ሰዎችን አስተባብራ እስር ቤት የቢገኙ እስረኞችን ወደ ሀገራቸው እንደገቡ የአየር ትኬት ቆርጠው ለመተባበር ጥረት አረገች፡፡ ይሄ ዲያቆን በፍጹም ብሎ መንገድ ዘጋ፡፡ ለእኔ ነግራኝ አናገርኩት፡፡ ፈጽሞ ሊሰማኝም ሊረዳኝም አልፈለገም፡፡ በራሄል ዘገየ ያላሰለሰ ጥረት የተወሰኑ ልጆች ለሀገራቸው በቁ፡፡ በዚህ ሰው ያልተከፋ፣ ያላዘነ፣ ያልተገፋ የለም፡፡ ግፋ ቢል ከ15 በላይ ሰዎች ለእኔ ቅሬታቸውን ነግረውኛል፡፡ ከዛ ውስጥ አንዷ የልደታ ቀብራራ ነኝ በሚል ስም የምትጠቀም እህቴም ታሪኳን ልካልኛለች፡፡ ቀጥሎ ላቅርበው፡፡
ሰላም ላንት ግሩም ያለውት ቤሩት ነው፡፡ ከመጣሁ 6 አመት ጨርሼ ሰባተኛዬን አጋምሻለሁ። በእነዚህ አመታት ግን የኢትዮጵያን ኤምባሲ እርዳታ የጠየኩበት መጥፎ ቀንን አልረሳውም፡፡ እዚህ እንደመጣሁ ለ1 አመት ያህል ከሴትዮዬ ጋር በፀብ ነው ያሳለፍኩት፡፡ መንስኤው ደግሞ ደሞዝ አለመስጠት ነው፡፡ ወር ሙሉ ሰርቼ ለዛውም 24 ሰአት ግን የደከምኩበት የላቤን ውጤት አይደለም ልቆጥረው በአይኔም አላየውም፡፡ ታዲያ ሰዎቼ በየወሩ ብሬን ስል ደብተር ይዛ ነው የምትምጣው፡፡ መጀመርያውን ወር ጠየኩ ከሁለት ወር በኋላ አንድ ላይ ትልኪያለሽ ስትል እሺ አልኩ፡፡ ሁለተኛው ወር ደረሰና ጠየኩ አሁንም መልሱ አንድ አይነት ሆነ፡፡ እኔ በራሴ እየፃፍኩ አስቀምጣለሁ፡፡ ሴትዮዋም በምታመጣው ደብተር ታስፈርመኛለች፡፡ እያለም 5 ወር ደፈንኩ።
አሁን ስጡኝ እስከዛሬ ለናቴ ከመጣሁ ገንዘብም አላኩ፣ ስልክም አልደወልኩም፡፡ ስለዚህ ደሞዜን ስጡኝ አልኩ፡፡ እሺ ብላ የስልክ ብር 10 $ ሰጠችኝና መደወያ ቦታ ይዛኝ ሄደች፡፡ እናቴ እና ታናናሾቼን አናግሬ ሳልጨርስ ስልኩ ተቋረጥ፡፡ ደግሜ ልሞክር ብል አይሆንም ይበቃል ብላ እንደ ህፃን ልጅ እጄ እየጎተተች አስወጣችኝ። ታድያ እኔ የስልክ ብር ስትሰጠኝ ደሞዜንም ዛሬ ትሰጠኛለች ብዬ ጠበቅኳት፡፡ ግን የለም፡፡ መልሷ አሁንም እያጠራቀምኩልሽ ነው ሆነ፡፡
የሚገርምህ ለስልክ መደወል በ3 ሳምንት 1 ጊዜ ይዛኝ ትወጣለች፡፡ እሱንም ከኪሷ ሳይሆን ከገንዘቤ እየተፃፈ እደውላልው። አንድ ቀን። ህፃኗ ልጅ አልበሜን ስታይ እህቴና እኔ አብረን የተንሳነውን ፎቶ አየችው፡፡ ለአባቷ አሳየችው፡፡ ተጠራሁና ሄድኩ፡፡ ከእህትሽ ጋር ትመሳሰላላችሁ መንታሽ ናት ወይስ ደብል አርገሽ አሰርተሸ ነው ብሎ ጠየቀኝ፡፡ መንትያ መሆናችንን ገልጨለት ተመለስኩ፡፡ ሊያመጣት ስለሚፈልግ ፍቃዷን ጠይቂ ሲለኝ አላመነታሁም፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚባል ስለማላይ ጓጓሁ፡፡
የእሷንም ፓስፖርት በፋክስ ተላከና ፕሮሰሱ ተጀመረ። ለእኔ ግን አንድም ጊዜ ደሞዝ አልተሰጠኝም። 8 ወር ሞላኝ እህቴ አልቆላት መጣች፡፡ ግን አላየዋትም፡፡ ያመጣት ጓደኛው ቤት ነበር፡፡ መምጣቷንም በሳምንቷ ነው የነገሩኝ፡፡ እህቴን አገናኙኝ ብዬ ደውለው አገናኙኝ፡፡ ለ 5 ደቂቃ ብቻ። ብዙም ሳናውራ ተዘጋ፡፡
የደሞዜ ነገር ባይ አይሰጡኝም ብጨቃጨቅም ሳይሰጡኝ 10 ወር ሞላኝ፡፡ በቃ አልሰራም ቢሮ ልሂድ ብዮ እንዲወስዱኝ ተናገርኩ፡፡ ጠዋት ተነስቼ ለባበስኩና ቁጭ አልኩ፡፡ ሴትዮዋ መጣች፡፡
‹‹ለምን ቁጭ አልሽ ልጆቹን ቀስቅሰሽ አታለብሽም..›› ብላ አፈጠጠች፡፡ መስራት እንደማልፈልግና ስራዬ እንዳልሆነ ገልጨላት ተነስቼ ክፍሌ ገባሁ ።ልጆቹን እልብሳ ት/ቤት ልካ ተመልሳ መጣች፡፡ ‹‹..ለምን አትሰሪም..›› በማለት ጠየቀች የእኔ መልስ ግን አልሰራም ነበርና ባልዋን ቀስቅሳ ነገረችው፡፡ አይኑን እየጠራረገ
‹‹ለምን አትሰሪም ምን ሆነሽ ነው የማትሰሪው..›› አለ፡፡ ካከፈላችሁኝ መስራት አልፈልግም ቢሮ ውሰዱኝ ወይ አገሬ ላኩኝ አልኩ፡፡ በእዚህ ሰአት ነበር የእህቴን ከመጣበት ቤት መጥፋት የሰማሁት፡፡ ጭራሽ ባሰብኝ ተነስተን ቢሮ ሄድን፡፡ አገሬ ላኩኝ ወይ ቤት ቀይሩኝ ብል 11 ወር ምንም ሳልከፈል ሰርቼ ይባስ ብሎ 2500$ ክፈይና የፈለግሽውን አድርጊ ብሎኝ አረፈ-ደላላው። የመጣሁበት ቢሮ 1 ሀበሻ አለች እሷና አክስቴ ጓደኛሞች ናቸው ለምኜ እንድትደውልልላት አደረግኩ፡፡ እነሱ ጋር ባለው ብር ላይ እንደምትጨምርና ነፃ እንደምወጣ እስከዛው እንድሰራ ነግራኝ ተዘጋ፡፡ እዛው ቢሮ ለ3 ቀን አደርኩኝ፡፡
የታፈችው ረዘም ያለ ነውና በሁለተኛ ዙር ብመለስ ፈለግሁ፡፡ ብዙዎች ቢሮ ማደር ችግር እንዳለው ሲናገሩ እሰማለሁ…..
ከአንድ ሰዓት በኋላ እመለሳለሁ፡፡

Post has attachment
Photo

Post has attachment
አሳዛኝ ዜና
በየመን ነገሩ አነጋጋሪ ሆኗል

1000 ኢትዮጵያዊያን ታፍነው ለውጊያ ተሰልፈዋል

በግሩም ተ/ሀይማኖት
የየመን ደህንነት ጥበቃ ባለስልጣን በአለፈው ረቡዕ ‹‹..1,000 የኢትዮጵያ ስደተኞች በእስር ቤቱ ጠባቂዎች እርዳታ ከደቡባዊ የመን አጠቅ እስር ቤት አመለጡ..›› በማለት በፈገግታ ተሞልተው ለውጭ መገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጡ።
እስር ቤት ሰብረው 1000 ኢትዮጵያዊያን ጠፉ የሚለው አስገራሚ መግለጫቸውን ተከትሎ መገናኛ ብዙሀን ዜናው አራገቡት። ሀሙስ እለት እኔም በጀርመን ድምጽ ሬድዮ(ዶቼዌሌ) ዜና ማህደር ፕሮግራም ላይ ዘገባውን አቀረብኩ፡፡ ዝም ማለቱ አላስቻለኝም እና ከዜናው በኋላም ሁኔታውን ለማጣራት ሞከርኩ። ጉዳዩ የመን ውስጥ መነጋገሪያ ሊሆን ቀርቶ ውሾን ያነሳ ውሾ ሆኗል። አሁንም 1000 ኢትዮጵያዊያን የገቡበት ሙሉ ለሙሉ አልታወቀም። ግን ፍንጭ አለ። ፍንጩ ግን አስፈሪም አሳሳቢም ነው፡፡ ሀይ ባይ የሌለው ህዝብ ነውና ወደ ጦርነት እንደወሰዷቸው የደህንነት ባለስልጣናቱ ደጋግመው ይናገራሉ፡፡
የየመን ደህንነት ጥበቃ ባለሥልጣን ስለ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ሁኔታ ሲያስረዱ ‹‹..በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር የገቡ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው እየመለስን ነው። የምስራቅ አፍሪካ ስደተኞች በተለይም ኢትዮጵያዊያን ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ እንኳን ወደ ሀገራችን መግባት አላቆሙም። ጦርነቱ በተፋፋመበት የደቡብ የመን ክፍል ሁላ ነው የሚገቡት። ብዙ ጉዳትም እየደረሰባቸው ነው። (ብዙ ጉዳት ማለት ከአካል መጉደል አስከሞት ብሎም በተለያዩ ቡድኖች ተይዘው በግዴታም በመደለል በውዴታም ለውጊያ እየተዳረጉ መሆኑን ልብ ይባልልኝ፡፡ ወደ ባለስልጣኑ ንግግር ስመለስ) በተለያየ ቦታ ፖሊስ እየያዛቸው በየጊዜው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እያደረግን ነው። ባለፈው ወር መጨረሻ (ሴፕተምበር ማለታቸው ነው) ብቻ 220 ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው መልሰናል፡፡ ሁቲዎች እንደሚከሱን ስደተኞች በመመልመል አላሰለፍንም። በአሁኑ ወቅት ደግሞ 1,000 የኢትዮጵያ ስደተኞች በእስር ቤቱ ጠባቂዎች እርዳታ ከደቡባዊ የመን አጠቅ እስር ቤት አመለጡ በማለት አስታወቁ።
አንዳንዶች እንደሚሉት ታሳሪዎቹ 1,400 ኢትዮጵያውያን ናቸው። በእርግጥ የእስር ቤቱ መዝገብም ይሄንኑ ቁጥር ትክክለኛነት ያረጋግጣል። በትክክል ከእስር ቤት የጠፉት 1090 አካባቢ ሲሆኑ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ 220 የሚሆኑትን ወደሀገራቸው ማሳፈራቸውን የደህንነት ጥበቃ ባለስልጣኑ ስላስታወቁ ቀሪ ወደ መቶ የሚጠጉ እስረኞች አሁንም እስር ቤት መኖራቸውን አረጋግጫለሁ። ወደ ሀገራቸውም እንዲሄዱ ይደረጋሉ የሚል መረጃም አለ። አሁን እስር ቤት የቀሩት ሊያስመልጧቸው ያሉትን ሰዎች ሀሳብ ሳይቀበሉ ቀርተው እንደሆነ የቀሩት መገመት ይቻላል።
ከእስር ቤት አመለጡት የተባሉት ወይም በማምለጥ ስም የታፈኑት ኢትዮጵያዊያን ማሪብ የሚባል ቦታ ለውጊያ እንዲሄዱ የደህንነት ባለስልጣኑ በግልፅ ተናግረዋል፡፡ ጦርነቱን የሚሳተፉ ከተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ማሪብ እና ባይዳ በነዳጅ የበለጸጉ አውራጃዎች እነሱን ለመውሰድ እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች ጋር ተሻርከው እንዳስመለጧቸው ተናግረዋል፡፡ ከእስር ቤቱም እንደወጡ ተሽከርካሪዎች ቀርበውላቸው እንደተሳፈሩ ማወቃቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ማሪብ እና ባይዳ እስረኞቹ ከተወሰዱበት አጠቅ አጎራባች አውራጃዎች ናቸው፡፡ የፕሬዘዳንቱ ደጋፊዎች መቆጣጠር እነዚህን ቦታዎች መቆጣተር አልቻሉም፡፡ ‹‹..እነርሱ ዓመፀኞች ናቸው እየተዋጉ ነው..›› ሲሉም የደህንነት ጥበቃ ባለስልጣኑ ገልጸዋል፡፡ እዚህ የመን ውስጥ በሱማሌ በኩል አርገው በባህር በደቡብ የመን አደን፣ ሸቡዋና ቤራሊ የሚገቡትን የተለያዩ ተዋጊ ሀይሎች በመያዝ ለጦርነት ይዳርጓቸዋል፡፡ አላቃይዳ፣ ዳዓሽ(SISI)፣ የስደተኛው ፕሬዘዳንት አብዱረቡ ደጋፊዎች ስደተኛ ኢትዮጵያዊያንን በጦርነቱ ያሳትፏቸዋል ሲል የሁቲይ ራዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ይወቅሳል፡፡ ማረክናቸው ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንም በተደጋጋሚ በቲቪ አቅርበዋል፡፡
በጅቡቲ አድርገው በሞካም ሆነ በባብል መንደብ በኩል የሚገቡትን ኢትዮጵያዊያን በግሩፕ የተደራጁ አፋኞች ይዘው ከቤተሰብ ብር እንዲያስልኩ ያሰቃዩዋቸዋል፡፡ አካል ያጎድላሉ፣ ይገድላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ለአንድ ታጋች 6000 የሳዑዲ ሪያል ያስከፍላሉ፡፡ በኢትዮጵያ 48000 ብር አካባቢ ማለት ነው፡፡ ይህ ብር ካተላከ አይን ከማጥፋት ጀምሮ አካል ማጉደልን ጨምሮ እስከመግደል ያሰቃያሉ፡፡ በዚህ ተግባር ላይ የተሳተፉ በርካታ ኢትዮጵያዊያንም አሉበት፡፡ ከእነዚህ አጋቾች ሲታለፍ ሶስት አይነት እጣ ተንገፍጥጦ ስደተኛውን ይጠብቀዋል፡፡
አንደኛ፡- በስደት ያሉት ፕሬዘዳንት ደጋፊዎች የሁቲይ አማጽያንን ደጋግመው እንደሚከሱት ስደተኛውን እየያዙ ለጦርነት ይዳርጉታል፡፡
ሁለተኛ፡- ቦታው እስከ ሳዑዲ አረቢያ ድንበር ከፍተኛ የጦርነት ቃጣና በመሆኑ መመታት መሞት…በድንበር ጠባቂዎች መያዝ ….
ሶስተኛው፡- በጣም ጥቂት እድለኞች ከመቶ ሀያ ያህሉ ድንበሩን ጥሰው በሰላም ሳዑዲ አረቢያ ይገባሉ፡፡ ከመቶ አስሩ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ካምፕ ገብተው በሰላም ወደ ሀገር ይገባሉ፡፡ ልብ በሉ ከመቶ ሰባው የትም በጉዳትም በሞትም በመታፈን ለጦርነት በመማገድም ይቀራሉ፡፡
እባካችሁ እዚህ የከፋ ሞት የነገሰበት ቦታ እየመጡ ይህን አይነት ስቃይ እንዳይቀምሱ ሁላችንም ለምናውቃቸው እናስተላልፍ ሼር በማድረግም ለሁሉም ይሄን መረጃ እናዳርስ….
Photo

Post has attachment
በየቦታው እንዲህ ወድቀን እና ሞተን እስከመቼ?
Photo
Wait while more posts are being loaded